post-thumb

የእነ "አሸብር አዋጅ?"

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አዲስ በረቀቀው "የፌደራል ስፖርት አስተዳደር እና ልማት ረቂቅ አዋጅ" ዘሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ህዝባዊ የውይይት መድረክ ማካሄዱ ይታወሳልⵆ

በ30 ገፆች፣ በ10 ክፍሎቸ እና በ70 አንቀፆች የተሰናዳው አዋጁ: በሚንስትሮች ምክር ቤት እና በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የሚወጡት ተጨማሪ የማስፈፀሚያ ደንቦች እና መመሪያዎች ሲካተቱበት ይበልጥ የተደራጀ እና አሁን ላይ ግለፅ ያልሆኑ ነገሮችን የበለጠ የሚያጠራ እንደሚሆን ተሰፋ አደርጋለሁ::

የረቂቅ አዋጁን አጠቃላይ መንፈስ ለመረዳት ስሞከር ማንኛችንም አዲስ አሰራር/ህግ ሲወጣ እንደሚሰማን ሁሉ ተስፋ፣ ስጋት እና ቀጭት ውል ብለውብኛል:: መስመር በመስመር እንኳን ባይሆን ጠቅለል አድርጌ የተሰማኝን ሀሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ::

ተስፋ:

በዚህ በየአንዳንዱ ቅፅበት ነገሮች በፍጥነት በሚለዋወጡበት ጊዜ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በላይ ሳይሻሻል የቆየው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲን እንደሚያጠናክር የሚጠበቀውን ይህንን አዋጅ: ከረፈደም ቢሆን የሚያዘጋጅ አመራር በመምጣቱ እና ወደ ተግባር  በመግባቱ፣ 

የህዝብን የሰነበተ የስፖርት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በመሞከሩ፣ 

ዘርፉ በመንግስት በኩል ተገቢው ትኩረት እየተሰጠው መሆኑን በሚያሳይ መልኩ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ የብሔራዊ ስፖርት ምክር ቤት እንዲቋቋም በማድረጉ፣

ከዚህ ቀደም እምብዛም ትኩረት ያልተደረገባቸውን እንደ የስፖርት መሰረተ ልማት ደረጃዎች እና ፈቃድ፣ የስፖርት ፈንድ፣ የስፖርት ግልግል ጉባኤ፣ የሽልማት አሰጣጥ፣ የፀረ አበረታች ቅመሞች እና ብዙ ማብራሪያ የሚፈልገው የስፖርት ኢንቨስትመንት በአዋጁ መካተታቸው ተስፋ እንድሰንቅ ካደረጉኝ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው::

ስጋት:

መንግስት ይህንን አዋጅ ለማውጣት ያስገደዱት በስፖርቱ ውስጥ የተንሰራፉት እና ህዘብን ለከፍተኛ ምሬት የዳረጉት: ስልጣንን በአግባቡ አለመጠቀም፣ ከህግ ወጭ ሀላፊነት ላይ መክረም፣ ሙስና፣ ሌብነት፣ ከህግ እና አሰራር በላይ መሆን፣ የህግ እና የህሊና ተጠያቂነት ማጣት፣ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል፣ የህዝብ ሀብትን ማባከን፣ ውጤት ማጣት፣ ብሔራዊ ስሜት መጥፋት እና ሌሎችም ምክንያቶች እንደሆኑ እረዳለሁ:: መፍትሔ እንዲመጣም ወደ ተግባር መግባቱንም አደንቃለሁ::

ነገር ግን የአዋጁን ይዘት በአፅንዖት ለተመለከተ:

1. የተለጠጠ የመንግስት ቁጥጥር እና ጣልቃ ገብነት?

አዋጁ የስፖርትን በመሰረታዊነት 'ከፖለቲካ ነፃ መሆን' የሚገድብ እና ትንፋሽ የሚያሳጥር: መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚንስትር መስሪያ ቤቱ በኩል የስፓርቱን የዕለትተዕለት ስራን ሳይቀር እንዲቆጣጠር የሚያደርገው መስሎ ይሰማኛል:: ይህ ደግሞ ለተቀላጠፈ አገልግሎተ የማይመች፣ ለተጨማሪ ብልሹ አሰራር በር የሚከፍት እንዲሁም ከዓለምአቀፍ አሰራር ጋር የማይሄድ እና የጥቅም ግጭት የሚያስከትል ነው::

በተጨማሪም ስፖርቱን የሚመሩ ሀላፊዎች ከስፖርቱ እና አባላቻቸው ይልቅ መንግስትን እና የመንግስትን አቋም እንዲያስቀድሙ ለጫና የሚዳርጋቸው ይመስለኛል::

ከዚያ ይልቅ መንግስት ብሔራዊ የስፖርት ተቋማት በራሳቸው እንዲቆሙ ማገዝ፣ ሀብት እንዲፈጥሩ እና በአግባቡ እንዲያስተዳድሩ፣ ጠንካራ አደረጃጀት እና ላወጧቸው ህጎች ፈፅሞ የሚገዙ እንዲሆኑ የድጋፍ፣ ክትትል እንዲሁም ይህንን ሳይፈፅሙ ሲቀሩ ተገቢውን የዕርምት እርምጃ በጊዜው ቢወስድ ይመረጣል:: 

በጥቅሉ የስፖርቱን የበዛ በመንግስት ላይ ጥገኛ መሆን እንደማንደግፈው ሁሉ የመንግስትን የበዛ ጣልቃ ገብነትም ማበረታታት የለብንም::  እናም መንግስት ሆይ እጂህን አታስረዝም ሊባል ይገባል::

2. የማስፈፀም አቅም?

የባህል እና ስፖርት ሚንስትር  በዚህ አዋጅ እፈፅማቸዋለሁ ያላቸውን ተግባራት በሙሉ የሚተገብር ከሆነ ከአዋጁ መፅደቅ አስቀድሞ ወይንም እኩል የራሱን ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ የሚያስፈልገው ይመስለኛል:: ነገር ግን ተቋሙ አሁን ባለው የአሰራር ስርዓት እና የሰው ሀይል ይህንን አዋጅ ለመተግበር የሚሞክር ከሆነ: በግሌ ይፈፀም ይሆንን? የሚል ስጋት በትልቁ አለኝ::

ቁጭት:

ለአዋጁ መውጣት ከላይ የጠቃቀስናቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው: በዋናነት ግን በአለፉት ዓመታት በብሔራዊ ፌዴሬሸኖች አመራር ላይ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ: ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይኖራቸዉ: ከተቋም ወደ ተቋም ከህግ እና ህሊና ተጠያቂነት ውጭ: በብዙ ክሶች ታጅበው የዘለቁ እንደ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ያሉ የስፖርቱ አመራሮች: መንግስት በስርዓት አስከብራለሁ ስም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ነፃው የስፖርት አስተዳደር አለም እንዲገባ ምክንያት መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው::

ይህንን እንድል ያደረገኝ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ብዙ እንደሚተገበሩ የተገለፁ ስራዎች ወደ ፊት በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያወች ዝርዝር አፈፃፀም እንደሚወጣላቸው ሲገለፁ: እንደ ዶ/ር አሸብር አይነት ህግ የጣሰ፣ ማባበያ ሰጥቶ የተመረጠ ወዘተ... "ስፖርታዊ ማጨበርበር" የሚል ክስ የሚቀርብባቸው ሰዎችን ግን ያለ ተጨማሪ ደንብ እና መመሪያ በቀጥታ በአዋጁ አንቀፅ 67 ቁጥር 8 ከፍተኛውን የ10 አመት ፅኑ እስራት ቅጣት እንደሚጣልባቸው መገለፁ ነው::

ከረጅም ጊዜ ጥበቃ እና ዝግጅት በሗላ የረቀቀው ይህ አዋጅ በታዳጊዎች ልማት፣ ስፖርት ኮሜርሻላይዜሽን እና ዲፕሎማሲ፣ በክለቦች ልማት እና ደረጃ፣ የምርምር እና የልህቀት ማዕከላት ግንባታ እና አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ጠንካራ ጉዳዮች የግለሰቦችን አጀንዳ ያክል ትኩረት መነፈጋቸው ያስቆጫል::

አዋጁ በተወሰኑ ስፖርቶች እና ፌዴሬሽኖች ላይ ብቻ ያተኮረ ይመስላል:: 

የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ዋና የስልጣን ባለቤት የሆነውን ጠቅላላ ጉባኤ አወቃቀር እና የሀገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች አመሰራረት እና አሰራር ስርዓት ላይ በለሆሳስ ማለፉም ያስተክዛል::

በመጨረሻም የሁላችንም ፍላጎት ስፖርት ተገቢው ትኩረት ተሰጠቶት በህግ እና በስርዓቱ እንዲመራ፣ አጥፊዎች ከሜዳው ገለል እንዲደረጉ፣ ስፖርቱን የሚወዱ እና የሚያገለግሉ ሰዎች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ እንደሆነ አምናለሁ: በመሆኑም አዋጁ አሁን ከህግ እና ከህሊና ተጠያቂነት ውጭ በተለያዩ የስፖርት ማህበራት አመራርነት የተቀመጡ ሰዎችን ከቦታው ያስነሳልናል በሚል አሁኑኑ ካልተተገበረልን የምትሉ ሰዎች ነገሩን በጥንቃቄ ብታዩት የኋላኋላ "ተቀምጠን የሰቀልነውን ... እንዳይሆን፣ በሌላኛው ጫፍ ያላችሁ እና ከስልጣን ውጭ ሌላው ቢቀር የህዝብ ሀዘን እና ቁጭት እንኳን ለማይታያችሁ ደግሞ በኔ እምነት አዋጁ የወንድ በር እንደከፈታላችሁ ይሰማኛል እናም ተጠቀሙበት::

ሚንስትር መስሪያ ቤቱም ይህንን ወሳኝ ሰነድ በምክር ቤት አዋጅ አድርጎ ከማስፀደቁ በፊት: ልዩ ልዩ አስተያየት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ቢጨመሩ፣ ቢቀነሱ እና ቢሻሻሉ የሚሏቸው ነጥቦች የሚያካፍሉበትን ተጨማሪ መንገድ ቢያመቻች ጥቅሙ ለሀገር ነው ብየ አምናለሁ::



Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.